1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመርዓዊው ግድያ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ

ዓርብ፣ የካቲት 8 2016

በጎጃም መርዓዊ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ ያዘዙትና የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ ግፊት እንዲደረግ ዓለም አቀፉ የዐማራ ህብረት ጥሪ አቀረበ። ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው ህብረት፤ የመራዊው ግድያን ያዘዙትና የፈጸሙት ለዓለም አቀፍ ፍርድ መቅረብ አለባቸዉ፤ በዐማራ ክልል የተራዘመው የእስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት አለበት ሲል ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4cULa
ዓለም አቀፉ የዐማራ  ህብረት
ዓለም አቀፉ የዐማራ  ህብረትምስል Global Amara Coalition

የመራዊው ግድያን ያዘዙትና የፈጸሙት ለዓለም አቀፍ ፍርድ መቅረብ አለባቸው

የመራዊው ግድያ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ

በጎጃም መራዊ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ ያዘዙትና የፈጸሙት ለፍርድ እንዲቀርቡ ግፊት እንዲደረግ ዓለም አቀፉ የዐማራ  ህብረት ጥሪ አቀረበ።  ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው ዓለም  አቀፉ የዐማራ ህብረት ሊቀ ዶክተር ሺፈራው ገሠሠ፣ህብረቱ ሰሞኑን ስለጉዳዩ ያወጣውን መግለጫ አስመልክተው ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣ የመራዊው ግድያን ያዘዙትና የፈጸሙት ለዓለም አቀፍ ፍርድ መቅረብ አለባቸው። የህብረቱ የዲፕሎማቲክ ኮሚቴ ሊቀመንበር ወይዘሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ በዐማራ ክልል የተራዘመው የእስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጠይቀዋል።

"በጣም ዘግናኝ ግድያ"

ዓለም አቀፍ የዐማራ ህብረት፣ጎጃም በምትገኘው መራዊ ከተማ በተፈጸመው ግድያ፣ ከ200 የማያንሱ ንጹኀን ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ዐማራውን ለማጥፋት ታልሞ የተፈፀመ ባለው የመራዊ ከተማ ግድያ፣ከተገደሉት መኻከል፣ የ15 አመት ታዳጊ ወጣቶች፣የ95 ዓመት መነኩሴ እና የሃይማኖት አባቶች ይገኙበታል። በተጨማሪ፣ሁለት አብያተ ክርስቲያናት እና መጠነ ሰፊ የዜጎች ንብረት ውድመት እና ዘረፋ ተፈጽሟል ብሏል። የህብረቱ ሊቀመንበር ዶክተር ሺፈራው ገሠሠ፣በመራዊ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ "በጣም ዘግናኝ"ሲሉ ገልጸውታል። "በጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በመራዊ ከተማ ቤት ለቤት በመግባት፣ህፃን፣ ወጣት፣ ሽማግሌ አዛውንት፣ ነፍሰጡር የሆኑት የሃይማኖት አባቶች ሳይለይ፣እያወጣበቀይ ሽብር መንገድ ጊዜ እንደሚደረገው፣በደርግ ጊዜ እንደሚደረገው፣ርሸና ነው ያካሄደው። ፍጹም ዘግናኝ፣ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰበ በጣም ዘግናኝ የሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው የፈፀመው።"

ገለልተኛ ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድን ይሰማራ

የህብረቱ መግለጫ፣በመራዊ ከተማ  የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የሚያጣራ ገለልተኛ የዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድን እንዲሰማራና፣ የዘር ማጥፋት ላይ የተሳተፉትን በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል። ሊቀመንበሩ ይህን አስመልክቶ፣የሚከተለውን ተናግረዋል። "እነዚህን ወንጀለኞች፣ ትዕዛዝ የሰጡትንና ትዕዛዝ እንዲፈጸም  ያደረጉትን በሙሉ፣ በአለም አቀፍ ህግ መቅረብ መቻል አለባቸውፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸው።

የተራዘመው አስቸኳይ አዋጅ ጉዳይ

 ወይዘሮ ጽጌሬዳ ሙሉጌታ፣ የህብረቱ መስራችና የዲፕሎማቲክ ኮሚቴ ሊቀመነሰበር ናቸው፤የመራዊውን ግድያ አስመልክቶ በአስቸኳይ መፈጸም ስላለባቸው ጉዳዮች ያስረዳሉ።  "ጥቃት የተፈጸመባቸው ወገኖቻችን ካሳ እንዲከፈላቸው  ያስፈልጋል። ቤተሰብ አለ ልጅ አለ።አስቸኳይ አዋጁ ደግሞ በአስቸኳይ እንዲነሳ  እንፈልጋለን። ጦርነት የተጀመረው የዐቢይ ጦር ዐማራ የሚዘምተው ማቆም አለበት። ወንድምና ወንድም እየተጋደለ ነው።ነገሩን በጥሞና ስናየው እና ይሄ ሊጠቅመን አይችልም። በሙሉ የኅሊና እስረኞች ባሉበት አስቸጋሪ በሚባሉ እስር ቤቶች ውስጥ የታሰሩት ሁሉ በሰላም እንዲፈቱና ወደ ቤተሰቦቻቸው እና ወደኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ፣የትምህርት ሁኔታውም እንዲቀጥል፣ትምህርትም መማር አልቻለም በተለይ በዐማራ ክልል፣ሕዝቡ እንዲሁ ወደ ትምህርት ቤትም ሳይገባ በስራ ዕጥነት ከሰባ በመቶ በላይ እየተሰቃየ ነው ያለው ።"

ኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አስተያየት ለማግኘት ብንደውልላቸውም፣ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ለጊዜው አልተሳካም። ይሁንና፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስተር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ በትላንትናው ዕለት፣ "የመከላከያ ሃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ዒላማ አላደረገም" ሲሉ ለዶይቸ ቨለ ማስተባበያ መስጠታቸው ይታወቃል።

የአሜሪካ መንግስት በመራዊ ተፈጸመ የተባለው ግድያ፣እንዳሳሰበው  ግልጾ፣ ገለልተኛ የሆነ ምርምራ ያለገደብ እንዲደረግ ጠይቋል። የአሜሪካ መንግስት የመራዊውን ግድያ አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ በጎ ጅምር ያለው ዓለም አቀፍ የዐማራ ህብረት፣ ሌሎችም መንግስታት ተመሳሳይ አቋም፣መግለጫዎችና ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል። 

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ