1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseረቡዕ፣ መጋቢት 18 2016

ዐርዕስተ ዜና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሂሳብቸው ከተቀመጠ ገንዘብ ውጭ በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ወሰደው በከፊል ተመላሽ አደረጉ ያላቸው ግለሰቦች ቀሪውን ገንዘብ እስከ ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ካልመለሱ ማንነታቸውን በመገናኛ ብዙሀን ይፋ እንደሚያደርግ አስጠነቀቀ የባህር ዳር ከነማ የመሐል ሜዳ የእግር ኳስ ተጫዋች አለልኝ አዘነ የእግር ኳስ ቡድንኑ አስታወቋል። በዩናይትድ ስቴትሱ የሜሪላንድ ግዛት ዋና ከተማ ባልቲሞር የሚገኝ ድልድይ በመርከብ ተገጭቶ ከተደረመሰ በኋላ የደረሱበት አልታወቀም የተባለ ስድስት ሰዎች ፍለጋ ቆመ። የሕይወት አድን ሥራው ቆሞ ወደ አስከሬን ፍለጋ መገባቱን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4eCO7

አዲስ አበባ   የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስጠንቀቂያ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. በባንኩ የሲስተም ማዘመኛ ሥራ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም በሂሳብቸው ከተቀመጠ ገንዘብ ውጭ በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ወሰደው በከፊል ተመላሽ አደረጉ ላላቸው ግለሰቦች ተጨማሪ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ አወጣ ። ባንኩ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው ስማቸው፣ የሂሳብ ቁጥራችው እና ሂሳባቸው የሚገኝበት ቅርንጫፍ የተዘረዘረው 5166 ግለሰቦች ያላግባብ ከወሰዱት ገንዘብ በከፊል ተመላሽ ቢያደርጉም ቀሪውን ገንዘብ አለመመለሳቸውን ገልጿል። ባንኩ ቀደም ሲል ባስጠነቀቀው መሠረት ወደ ቀጣዩ ሕጋዊ ርምጃ ከማለፉ በፊት ቀሪውን ገንዘብ እንዲመልሱ ጠይቋል። ሆኖም እስከ ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ድረስ ገንዘቡን በሚመልሱት ላይ በባንኩ በኩል ቀጣይ ሕጋዊ ርምጃ እንደማይወሰድ ያረጋግጣል ብሏል። እስከተጠቀሰው ቀን ገንዘቡን የማይመልሱ ግን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎችን በመጠቀም ሙሉ ስማቸውን፣ ፎቷቸውን፣ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በመውሰድ ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ለሚመለከታቸው የሕግ አካላትና ተቋማት በማሳወቅ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስጠንቅቋል። እንዲሁም ከሕግ አካላትና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ቀጣይ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና የአስተዳደር ሕጋዊ ርምጃዎች እንደሚወሰድባችው የመጨረሻ ያለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለአግባብ ተወሰደብኝ ካለው ከ800 ሚሊየን በላይ ብር፣ ከ600 ሚሊየን በላይ ብር አስመልሻለሁ ብሏል። ገንዘቡን ከወሰዱት መካከል 15 ሺህ ገደማ የሚሆኑት በፈቃዳቸው ገንዘቡን መመለሳቸው ተገልጿል። የባንኩ ፕሬዝደንት አቤ ሳኖ ከተወሰደው ገንዘብ 80 በመቶው የሚሆነውን ማስመለስ መቻሉን ትናንት ተናግረዋል ።መጋቢት 6 ቀን፣ ወደ 14 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ወይ ከባንኩ በቀጥታ ወጥቷል ወይም በዲጅታል ስልት ወደ ሌላ የባንክ ሂሳብ ተዛውሯል ብለዋል የባንኩ ፕሬዝዳንት ። ቀደም ሲል ከባንኩ ያለአግባብ የወጣው ገንዘብ 40 ሚሊየን ዶላር ነው የሚሉ ዘገባዎች ወጥተው ነበር።  በጎርጎሪዮሳዊው 1963 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 40 ሚሊየን ደንበኞች ያሉት የሀገሪቱ ግዙፍ ባንክ ነው።

 

ጄኔቫ    አንድ የተመ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ አጥኚ ማስፈራሪያ ይደርስብኝን ነበር አሉ

 

በጋዛው ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸሟ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ የሚል ዘገባ ያቀረቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ልዩ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አጥኚ በሥራቸው ወቅት ማስፈሪያ ይደርሳቸው እንደነበር ተናገሩ ። እስራኤል በኃይል በያዘችው በዌስት ባንክና በጋዛ የሰብአዊ መብት ይዞታ አጥኚ ፍራንቼስካ አልባኔዜ ሥራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማሳለፋቸውንና ሁሌም ማስፈራሪያ ይደርሳባቸው እንደነበር ለተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ትናንት አስታውቀዋል። አልባኔዜ ዛቻና ማስፈራሪያው፣ አምነው በተቀበሉት ሥራና በውጤቱም ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም ብለዋል። ፍራንቼስካ ያቀረቡትን ዘገባ እሥራኤል ሙሉ በሙሉ ተቃውማለች። እስራኤል ፍራንቼስካ አልባኔዜን በሪፖርታቸው የእስራኤልን መመስረትና ኅልውና ሕገ ወጥ አድርገዋል ስትል ወቅሳ ነበር። ይሁንና ከጎርጎሮሳዊው 2022 አንስቶ በዚህ ኃላፊነት ላይ የሚገኙት ፍራንቼስካ የዛቻውን ምንነትም ሆነ ከማን እንደተሰነዘረባቸው አልተናገሩም።

 

 

ባልቲሞር  በባልቲሞሪ ድልድይ መደርመስ 6 ሰዎች ሳይሞቱ አልቀረም

 

በዩናይትድ ስቴትስ ሜሪላንድ ግዛት ዋና ከተማ ባልቲሞር የሚገኝ ድልድይ በመርከብ ተገጭቶ ከተደረመሰ በኋላ የደረሱበት አልታወቀም የተባለ ስድስት ሰዎች ፍለጋ ቆመ። ባለስልጣናት ፍለጋው የወሰደውን ጊዜ የተካሄደውን ጥልቅ ፍተሻ እና የውኃውን ቅዝቃዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰዎቹ በሕይወት ይገኛሉ ተብሎ እንደማይታመን አስታውቀዋል። በዚህ የተነሳም የሰዎቹ ፍለጋ እና የሕይወት አድን ሥራው ቆሞ ወደ አስከሬን ፍለጋ መገባቱን ገልጸዋል። የደረሱበት ያልተወቀው ድልድዩ ሲፈርስ በሥራ ላይ የነበሩ 6 የግንባታና ጥገና ሠራተኞች ነበሩ ከመካከላቸው ሁለቱ ከጓቲማላ መሆናቸውን የጓቲማላ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ሦስቱ ደግሞ ከሜክሲኮ መሆናቸውን የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አረጋግጠዋል። በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት ከሟቾቹ ውስጥ የሳልቫዶርና የሆንዱራስ ዜጎችም ይገኙበታል። ድልድዩ ሲፈርስ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ውሐ ውስጥ ሲወድቁ ከመካከላቸው የሁለቱን ሕይወት ማትረፍ ተችሏል። የበርካታ እቃ ጫኝ የንግድ መርከቦች መተላለፊያ በነበረው በዚህ መስመር ጉዞውን በመጀመር ላይ የነበረ አንድ እቃ ጫኝ መርከብ  ከትናንት በስተያ ሌሊት የድልድዩን አንድ ምሶሶ ከገጨ በኋላ ነበር በጎርጎሮሳዊው 1977 .. የተገነባው «ፍራንሲስ ስኮት ድልድይ» ከመቅጽበት የፈረሰው። የአሜሪካን የፌደራል ምርመራ ቢሮ እና ሌሎች መስሪያ ቤቶች አደጋውን ከአሸባሪነት ጋር የሚያያዝ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። የሚሪላንድ ግዛት ሀገረ-ገዥ ዌስ ሙር እስካሁን የተካሄዱ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች አደጋ መድረሱን ብቻ የሚያመለክቱ ናቸው ብለዋል። የድልድዩን መደርመስ እጅግ የሚያሳዝን ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባይደን ወደቡን መልሶ ክፍት ለማድረግና ድልድዩንም ለመገንባት ቃል ገብተዋል።

 

ሞስኮ  በካውኩሱ ጥቃት የሞትቱት ሰዎች ቁጥር 140 ደረሰ

ባለፈው ዓርብ ከሩስያ ዋና ከተማ ሞስኮ ወጣ ባለ ስፍራ በሚገኘው የካውኩስ የሙዚቃ አዳራሽ በተፈጸመ ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 140 መድረሱን የሩስያ  ባለሥልጣናት ዛሬ ተናገሩ። ባለስልጣናት እንዳሉት ዛሬ አንድ የአደጋው ሰለባ ሕይወት ካለፈ በኋላ የሟቾች ቁጥር ወደ 140 ከፍ ብሏል። ሟቹ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ሲረዱ ከነበሩት አምስት ሰዎች አንዱ ነበር። የሩስያ የጤና ሚኒስትር እንደተናገሩት በአደጋው የቆሰሉ 80 ሰዎች አሁንም ሆስፒታል ውስጥ እየታከሙ ነው።ሌሎች 205 ደግሞ ተመላላሽ ህክምና ላይ ይገኛሉ።ባለፈው ዓርብ የደረሰው የሽብር ጥቃት ከሀያ ዓመት ወዲህ በሩስያ ምድር የተፈጸመ ከባዱ የሽብር ጥቃት ተብሏል። ቢያንስ አራት አውቶማቲክ ጠመንጃ የታጠቁ ሰዎች በስፍራው በተሰበሰቡ በሺህዎች በሚቆጠሩ እድመተኞች ላይ ጥይቶችን በዘፈቀደ ከማርከፍከፋቸውም በተጨማሪ አዳራሹንም በእሳት አጋይተዋል።

 

አዲስ አበባ   የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ተጫዋች አለልኝ አዘነ አረፈ 

 

የባህር ዳር ከነማ የመሐል ሜዳ የእግር ኳስ ተጫዋች አለልኝ አዘነ አረፈ። አለልኝ አዘነ ትናንት ለዛሬ አጥቢያ ሲነጋጋ በአርባምንጭ ከተማ ድንገት ሕይወቱ ማለፉን የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ቡድን አስታወቋል።

የእግር ኳስ ቡድኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ፍቃዱ ዛሬ ከአዲስ አበባ ለዶቼቬለ በስልክ እንደተናገሩት ተጫዋቹ ትናንት ለዛሬ አጥቢያ አነጋግ ላይ ሕይወቱ በድንገት አልፏል። የቀብሩ ስነስርዓትም ዛሬ በተወለደበት በአርባምንጭ ከተማ መፈጸሙን ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ገልጸዋል፡፡

«እኛም ሌሊት ነው የሰማነው ሕይወቱ ማለፉን። እዚያ ያሉ ሰዎች ደውለው ነው የነገሩን። ባህር ዳር ከነማ የስፖርት ክለብ ነበር እየተጫወተ ያለው። ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ተጫውቷል። በተለይ ጉልበቱ ላይ የነበረ ህመም ነበር። እረፍት ተሰጥቶት አርባ ምንጭ ነበር።»

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ቀኑ ዛሬ 6፡30 ድረስ የተጫዋቹ ሞት ምክንያት እንደማይታወቅ አቶ ልዑል ገልጠዋል፡፡ አለልኝ አዘነ ከዚህ ቀደም  ለአርባ ምንጭ ታዳጊ የእግር ኳስ ቡድንና ለአርባ ምንጭ ከነማ፣ ለሐዋሳ አግርኳስ ከነማ፣ አሁን ደግሞ ለባሕር ዳር ከነማ እግር ኳስ ቡድን የመሐል ተጫዋች ነበር፡፡ ተጫዋቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ተጫውቷል፡፡ አለልኝ አዘነ ትዳር የመሰረተው በቅርቡ እንደነበርም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የ26 ዓመቱ አለልኝ አዘነ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአርባምንጭ ከተማ ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት መፈፀሙን አለምነው መኮንን ዘግቧል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
Mittelmeer | Asylreform in der EU
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።